YT_TheGeneration

                                                                            YaTewlidTheGeneration

ያ ትውልድ ድረ ገጽ ምሥረታ አስመልክቶ

ያ ትውልድና ሜይ ዴይ

የዛሬ 35 ዓመት አርብ ሚያዝያ 21 ቀን 1969 ዓ.ም. በመላዋ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርት (ኢሕአፓ) ዓለም አቀፍ የሠራተኞችን ቀን፡ ሜይ ዴይ ምክንያት በማድረግ አባላቱና ደጋፊዎቹ በየአካባቢያቸው በሰላማዊ ሰልፍ የተነሱበትን ዓላማ በማስተጋባት የትግል አንድነታቸውን ለመግለጽ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ለሰልፍ ተንቀሳቀሱ።

ደርግ ከጥር 26 ቀን 1969 ዓ.ም. የመንግሥቱ ኃ/ማርያም በተለይ በኢሕአፓ ጥላ ሥር የተሰለፉ፡ የደገፉ፡ ያዩ፡ ያለፉትን ከሕፃናት እስከ አዛውንት ደም በማፍሰስ የበላይነቱን ለማረጋገጥ፡ ደም የተሞላ ጠርሙስ "በአብዮት" አደባብይ ከሰበረ በኋላ የቀይ ሽብር ድህረ ዝግጅት “ነፃ እርምጃ” የበርካታዎችን ሕይወት በየደቂቃው እየነጠቀ ያለፈበት ፋሽስታዊ ወቅት ነበር።

ዓለም አቀፍ የላብ አደሩን ቀን ሜይ ዴይ 1969 ዓ.ም. ከደርግ ልቅ ያጣ ጭፍጨፋ አንፃር በዕለቱ ማክበር እንደማይቻል የተገነዘበው ኢሕአፓ፡ ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ ለኢትዮጵያ ሀገሩና ለጭቁን ሕዝቦች ያለውን ታማኝነትና የዓላማ ጽናትና ቆራጥነት ለማረጋገጥ የተዘጋጀው የሚያዝያ 21 ቀን 1969 ዓ.ም. ሰልፍ ከድርጅቱ እየከዱ ወደ ደርግ መግባት በጀመሩ አንጃዎች ሙሉ መረጃ ለደርግ በመድረሱ መንግሥቱ ኃ/ማርያምና ጀሌዎቹ አብዮት አደባባይ በምሳሌነት ያፈሰሱትን ደም ሊጠጡ ቋምጠውና አድፍጠው ታጠባበቁ።

ሰልፉ ሲጀመርና የጥይት ሩምታ ሲለቀቅ እኩል ሆነ። በርካታ ሕፃናትና ወጣቶች "ፍጹም ነው እምነቴ" እንዳሉ ሕይወታቸውን ለትግሉ ሰጡ። አዲስ አበባ የደም ዳመና አንዣበበባት። በየአካባቢው ምሽቱ ደም በጠማቸው የደርግ ገዳዮች ሽብር ሆነ። ማ ይሙት ማ ይትረፍ መለየት እስኪያቅት ተኩስና ለቅሶ ለሊቱን አድረውበት፡ ለተረኛው ንጋት ለቀቁ። ነጠላዎች ተዘቀዘቁ፡ ቀሚሶች ጥቁር ሆኑ፡ እናቶች አባቶች ሀዘን፡ ቁጭትና እየዬ ዋጣቸው። ልክ የዛሬ 35 ዓመት።

አብረን ተሰልፈን፡ አብረን ጮኸን፡ አብረን ታግለን፡ አብረን ተሰቃይተን በተለያየ አጋጣሚ ዛሬ በሕይወት ያለን የዚያ ትውልድ አባላት ቢያንስ ልንዘክራቸው፡ ልናስባቸው ይገባል። ደማቸውን ያፈሰሱ አጥንታቸውን የከሰከሱት "ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም" "የዴሞክራሲ መብት ያለገደብ ለሁሉም" እየፈከሩ፡ "ደሀ ደሀ ምን ታየበት፤ እንዳይማር የሆነበት" እየዘመሩ፡ ለሕዝብና ለሀገር እንደጮሁ፡ መሆኑን በመመስከር ታሪካቸው ታሪካችን፡ ደማቸው ደማችን ነውና፡ እነሱን እያስታወስን አኩሪ ተጋድሏችንን ከታሪክ በራዦችና ጥላሸት ቀቢዎች በመጠበቅና በመከላከል ቀጣዩ አዲስ ትውልድ እነማን እንደነበርንና ምን ሠርተን እንዳለፍን ግንዛቤ በማስጨበጥ ከእኛ ሊቀስም ከሚችለው ትምህርት በመውሰድ ሀገሩንና ሕዝቡን አፍቃሪ ብቁ ዜጋ ይሆን ዘንድ ማዘጋጀት ይጠበቅብናል።

የዚያን ትውልድ ታሪክ ማሰባሰብና ለታሪክ ተመራማሪዎች፡ ፀሀፊዎችና ለተተኪው ትውልድ ማስረከብ አንዱ ተልዕኮው አድርጎ የተነሳው የዚያ ትውልድ አካል የዛሬን ቀን በማስታወስ ለሀገራቸው ሉዓላዊነትና ለሕዝባቸው ክብር ሲሉ በተለያዩ አገዛዞች መስዋትነት ለከፈሉና እየከፈሉ ላሉ እንዲሁም በኢሕአፓ ጥላ ሥር ተሰልፈው በትውልድ መመተር ቀይ ሽብርና ነፃ እርምጃ ለወደቁት ወገኖቻችን መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ያ ትውልድ ድረ ገጽ (yatewlid.org or yatewlid.com) ከዛሬ ሚያዝያ 21 ቀን 2004 ዓ.ም. (April 29, 2012) ጀምሮ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አበርክተናል።

ያ ትውልድ ድረ ገጽ፡

 • 2630 የቀይ ሽብር ሰማዕታት ስምና 338 የቀድሞና የደርግ ባለሥልጣናት እንዲሁም በተለያየ ምክንያት የተገደሉ ስሞች በድረ ገጹ ገብተዋል
 • ወደ 300 የሚሆኑ የቀይ ሽብር ሰማዕታት ፎቶ በድረ ገጹ ተካቷል
 • ለማግኘት የተቻሉትን የኢሕአፓ ልሳን “ዴሞክራሲያ” 110 ዕትሞች ድረ ገጹ ውስጥ ተካተዋል
 • ሌሎች የኢሕአፓ ዕትሞች፡ መልዕክተ ኢሕአፓ (17 እትሞች)፡ ማን ያውራ የነበረ (ከቁጥር 1-15)፡ ፍካሬ (ቁጥር 16 እና 17)፡ አደራ (ቅጽ 2 ቁጥር 3 እና 4) የተገኙት በተመሳሳይ መልኩ ወደ ድረ ገጹ ተካተዋል
 • ድርጅቱ ከተከፈለም በኋላ በኢሕአፓ ዴሞክራሲያዊ በኩል የወጡት 8 ዴሞክራሲያ ዕትሞች፡ ዜና ኢሕአፓ 4 ዕትሞች፡ ፈለገ ዴሞክራሲ 1 ዕትም ድረ ገጹ ገብተዋል
 • የመኢሶን ልሳን የነበረው “የሰፊው ሕዝብ ድምጽ” 3 ዕትም በድረ ገጹ ተካቷል
 • በቀጣይነት የሌሎች የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች መረጃዎች ይካተታሉ
 • ይበልጥ ስለ ድረ ገጹና ዓላማችን ለመረዳት ድረ ገጹን ይጎብኙ። አስተያየትም ይስጡን (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

የተከበራችሁ ወገኖች የሰማዕታቱ መታሰቢያ ድረ ገጽ ለጊዜው በአገኘነው መረጃ የተዘጋጀ በመሆኑ፦

 • ያልተካተቱ ወገኖች ካሉ (እስካሁን ያገኘነው በጣም ጥቂቱን እንደሆነ እናምናለን)
 • የስም ስህተት ካለ
 • ስማቸው የተካተተው የተሟላ አድራሻ ካላችሁ
 • የሰማዕታቱ ፎቶ ያላችሁ
 • ተጨማሪ መረጃ ያላችሁ
 • የምታውቁት የመረጃ ምንጭ ካለ
 • በስህተት በሕይወት ያሉ ተጽፈው ከሆነ

በአጠቃላይ ይህ ድረ ገጽ ሊሟላና ሊዳብር የሚችለው በተለይ በሕይወት ባሉት የዚያ ትውልድ አባላት ትብብርና ድጋፍ በመሆኑ ማንኛውንም አስተያየታችሁንና ትብብራችሁን  ትልኩልን  ዘንድ  በትህትና  እንጠይቃለን።

በመጨረሻም ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች፡ ሲቪክ ማህበራት፡ ምሁራን፡ ታዋቂ ግለሰቦች፡ ወጣቶች፡ ሴቶች እህቶቻችን፡ አዛውንት እናቶችና አባቶች ትብብራችሁንና ድጋፋችሁን እንጠይቃለን።

የዚያን ትውልድ አኩሪ ታሪክ ለትውልድ ለማስተላለፍ ሁላችንም እንተባበር!

ያ ትውልድ

እትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

Long Live Ethiopia!

......ያ ትውልድ......
ታሪካችሁ ህያው ነው!

The Generation is Immortal!

 

እኛን ማግኘት/Contact us

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

703 300 4302